Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ አንድምታዊ ትርጉምን ለመረዳት ተማሪዎች የሚጠቀሙበት የአንብቦ መረዳት ብልሃቶችን መተንተን ነው፡፡ጥናቱ የተኪያሄደው በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ደጃዝማች በልቻ አባነፍሶ ሁለተኛ ደረጃና መሠናዶ ትምህርት ቤት በ2011 ዓ.ም በመማር ላይ ያሉ 750 በ15 ክፍሎች ከተመደቡ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በቀላል ዕጣ ናሙና አመራረጥ ዘዴ “9” ሰባት ተመርጧል፡፡ እንዲሁም አፍሪካ ህብረት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዘጠነኛ ክፍል በመማር ላይ ያሉ 320 ተተኳሪ ተማሪዎች መካከል በቀላል ዕጣ ናሙና “9” ሦስት ተመርጧል፡፡ በሁለቱም ትምህርት ቤቶች በድምሩ1092 ተማሪዎች መካከል 92 ተማሪዎች በቀላል ዕጣ ናሙና ተመርጠዋል፡፡ ይህን አላማ ለማሳካት በፈተና፣ በምልከታ፣ በጹሑፍ መጠይቅ እና በቃለ መጠይቅ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ የጥናቱን መረጃዎች ለመተንተን ገላጭ መረጃ መተንተኛ ስልት በተግባር ላይ ውሏል፡፡ የተሰበሰበው መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ ትንተና ተደርጎበታል፡፡
ከመረጃዎቹ የተገኙት ውጤቶች የሚያመላክቱት አንድምታዊ ትርጉምን ለመረዳት ተማሪዎቹ የተጠቀሙባቸው ብልሃቶች በአራቱ የአንብቦ መረዳ ንዑሳን አከፋፈል መሰረት በቀጥተኛ ብልሃቶች ስር ከተዘረዘሩት ቴክኒካዊ ድጋፍን ከሚሰጡ ስድስት ብልሃቶች አራቱን ተጠቅመዋል፡፡ እነሱም ግርፍ ንባብ አንባቢ የአንድን ጹሑፍ መልዕክት ወይም ፍሬ ነገሮችን ለማወቅ ሲል ጹሑፉን ከዳር እስከ ዳር ዐይንን በፍጥነት በማንቀሳቀስ ቶሎ ቶሎ የማንበብ ብልሃት፣ አሰሳ ንባብ ቁንጽል መረጃን ለመፈለግ ዐይንን በፍጥነት በማንቀሳቀስ ማንበብ፣ በምንባብ ወይም በምንባቡ ጥያቄ ላይ አንባቢው ትኩረት በሚሰጥባቸው ቃላት ወይም ሐረጋት ግርጌ ማስመር ወይም የተለየ ምልክት ማድረግ እና የቃል አገባባዊ ፍቺን መጠቀም ይኸውም አንባቢው በንባብ ሂደቱ የሚያጋጥሙትን እንግዳ ቃላት ፍቺ ለመረዳት ከአውዳቸው ተነስቶ ግምት ሲሰጥ የሚሉትን ነው፡፡ማብራራት እና ማጠቃለልን ከሚጠይቁ ስምንት የአንብቦ መረዳት ንዑስ ብልሃቶች ውስጥ የተጠቀሙባቸው አራት ናቸው፡፡ እነሱም የቋንቋውን የቃላት አሰላለፍ በራስ አባባል መረዳት፣ ከባድ ቃል ሲያጋጥም በራስ አባባል መገንዘብ፤ የቃላት ሰዋሰዋዊ ትርጉም ከምንባቡ ለማግኘት ሲል በንባብ ሂደት የሚያጋጥሙትን ወሳኝ ቃላት ለመረዳት ሙከራ ማድረግ፣ ሥዕላዊ መግለጫዎችን መመርመር የሚሉትን ብልሃቶች ተጠቅመዋል፡፡ ግጥምጥምነት እና መመርመርን ከሚጠይቁ አስራ አንድ ብልሃቶች ተማሪዎቹ የተገለገሉባቸው አምስት ሲሆኑ እነሱም የምንባቡን አጠቃላይ አካሄድ የታሪኩን ቅደም ተከተል በመያዝ መለየት፣ ከታሪኩ ጋር ቁርኝት ያላቸውን መረጃዎች መጠቀም፣ ቀጥሎ ስለሚመጣው ሃሳብ ግምት መስጠት፣ ቀጥሎ ስለሚከናወነው ነገር መላ መምታት፣ የታሪኩን መዋቅር መለየት እና የተለያዩ መረጃዎችን ማዛመድ ናቸው፡፡ በኢቀጥተኛ ብልሃት ስር ከተገለጸው አንብቦ መረዳት እና መቆጣጠርን ከሚጠይቁ አስራ ሰባት የአንብቦ መረዳት ንዑስ የብልሃት አከፋፈሎች ውስጥ ተማሪዎች የተገለገሉባቸው ስድስት ብልሃቶችን ነው፡፡ እነሱም መልስን ማዘግየት፣የንባብ ፍጥነትን መቀየር፣ግልጽ ያልሆነን ሃሳብ መለየት ፣በስህተት የተረዱትን ሃሳብ ተመልሶ ማረም፣ከዓላማ አንጻር አላስፈላጊ የንባብ ክፍልን መዝለል እና ችግር ሲያጋጥም ችግሩን ለመቅረፍ የራስ የሆነ መፍትሄ መስጠት ናቸው፡፡ አስራ አንድ ብልሃቶችን ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡
እንዲሁም ተማሪዎች የተጠቀሙባቸው ብልሃቶች ከጸሐፍት ንድፈ ሃሳብ ጋር በከፊል የሚመሳሰሉ ሲሆን በአንፃሩ አብረው የማይሄዱ ብልሃቶችም እንዳሉ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በምዕራፍ ሁለት ብልሃቶችን ለመጠቀም ተፅዕኖ የሚያስከትሉ የትምህርት ደረጃ፣የምንባቡ ሁኔታ፣የቋንቋ አጠቃቀም ችሎታና ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ብልሃቶች እንደሆኑ ከተገለጸው ንድፈ ሃሳብ ጋር መመሳሰልን እንዳሳየ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አንድምታዊ ትርጉምን ለመረዳት ተማሪዎቹ የተጠቀሙባቸው ብልሃቶች ማገዝ አለማገዛቸውን በተመለከት ቀጥተኛውን የአንድምታ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በልሃቶቹ የረዱ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ማደራጀት እና መተርጎምን በተጨማሪም መመርመርን የሚጠይቁ አንድምታ ጥቄዎችን ግን በከፊል ለመመለስ ብልሃቶቹ ቢያግዙም በአብዛኛው ግን አለማገዛቸውን የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ አንብቦ መረዳትና ብልሃቶች እጅግ የተቆራኙ እንደሆኑ የብልሃት ዕውቀት ብቻ የአንድምታ ትርጉምን ለመረዳት ብዙም ጠቀሜታ እንደሌለው የቀደመ ዕውቀት ወሳኝ እንደሆነ በማስገንዘብ በአንብቦ መረዳት ብልሃት አጠቃቀም ዙሪያ የታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስልቶች በመፍትሄ ሃሳብ ስር ተጠቁመዋል፡፡